RSS

ሊበራል ዲሞክራሲን !

25 Oct

 

ሊበራል ዲሞክራሲን ለምን ወያኔ ፈራው

ለመሆኑ ሊበራል ዲሞክራሲ ምንድነው?

ሊበራል ዲሞክራሲ ውልደትና እድገት በአውሮፓ በ18ኛ ክ/ዘመን መሆኑ ይነገራል፡፡ የሊበራል ዲሞክራሲ ዋና መገለጫው የሊበራሊዝም ፅንሰ-ሐሳቦች ማእከል ማድረጉ ሲሆን ይህም በዋናነት የግለሰብ ነፃነት ዋና እምብርቱ ነው፡፡ በመገለጫነትም ነፃ ፍትሓዊና አወዳዳሪ ምርጫዎችን ማስኬድ፣ የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት፣ የሕግ የበላይነት፣ የዲሞክራሲና ነፃነት መብቶችን ማክበር፣ ፍትሕን ማስፈን ወ.ዘ.ተ ያጠቃልላል፡፡ ሊበራል ዲሞክራሲ በርካታ ዐይነት የመንግስትና የሕገመንግስት አወቃቀሮች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ለአብነት፡ ሪፓብሊካዊ (እነ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ህንድ፣ ጣልያን ወ.ዘ.ተ)፤ ንጉሳዊ ሕገ-መንግስት (ጃፓን፣ ስፐይን፣ ሆላንድ፣ እንግሊዝ)፤ ፕሬዚደንታዊ (አሜሪካ፣ ብራዚል፣ ሜክሲኮ፣ አርጀንቲና)፤ ፓርላመንታዊ ስርዐት(አውስትራልያ፣ ህንድ፣ ፓኪስታን፣ ፖላንድ ወ.ዘ.ተ)፡፡

ከላይ እንደተገለፀው የሊበራል ዲሞክራሲ ዋና መገለጫ የግለሰብ ነፃነት ማክበር ነው፡፡ ሊበራል ዲሞክራሲ በአውሮፓ የነበሩ ጨቋኝ ንጉሳዊ አገዛዞችና ፈላጭ ቆራጮችን አደብ ለማስገዛት ነበር በጊዜው የነበሩ የአብርሆት ዘመን ምሁራን (enlightment intellectuals) የተመሰረተው፡፡ መሰረታዊ መርሁ ሰው ሁሉ እኩል ነው ብሎ የተነሳው እንቅስቃሴ የነአሜሪካና ፈረንሳይ አብዮቶችን አቀጣጠለ፣ ቀስ በቀስም ዐለምን ሁሉ አዳርሶ አብዛኛውን የዐለም ህዝብ የሚጠቀምበት ስርዐተ-ማሕበር ሊሆን ችሏል፡፡

ሊበራል ዲሞክራሲ የመንግስትን የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ሞራላዊ ጣልቃ ገብነት በእጅጉ የሚቀንስና እጁ እንዲያነሳ የሚያስገድድ ነው፡፡ ይህም ኢኮኖሚው ለገበያው አሳልፎ እንዲሰጥና ገበያው እራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር የሚያደርግ ነው፡፡

ከቀድሞዎቹ እነ ማርክስ፣ ሌኒን፣ አሁን ደግሞ እነ ናኦም ቾምስኪና ኤድዋርድ ሀርማንና መሰሎቻቸው ሊበራል ዲሞክራሲን የሐብታሞች መጨቆኛ መሳርያ ነው ብለው ቢከራከሩም ሊበራል ዲሞክራሲ ግን ግለኝነትና ስግብግብነት እየጨመረባት ባለችው ዐለም ውስጥ አሁንም ይሁን ለወደፊቱ ገዢ ሐሳብ ሆኖ መዝለቁ አይቀርም፡፡

ሊበራል ዲሞክራሲ የብዙዎቹ ያደጉና በፍጥነት እያደጉ ያሉ አብዛኛዎቹ የዐለም ሐገራት የሚመሩበት ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊቷ ማሊ ደኽይታ ጨቋኛ ቻይና ስበለፀገች መሰል ቁንፅል አብነቶች እያመጡ ዲሞክራሲን ከልማት ጋር ነጣጥሎ ለማየት መሞከር የከፋ ስህተት ላይ ይጥላል፡፡ 90 % ሐቅ የሚያመለከተው ዲሞክራሲና ብልፅግና ለያይቶ ማየት እንደማይቻል ነው፡፡

ኢህአዴግ ሊበራል ዲሞክራሲ አብዝቶ የሚጠላበት ምክንያት ሊበራል ዲሞክራሲ ፈጣን እድገት ስለማያመጣ አይደለም፡፡ አፍሪካ ውስጥ በፍጥነት እያደጉ ያሉና የአብዛኛውን የህዝባቸው ጠጠቃሚነት ያረጋገጡ ብዙዎቹ ሀገራት በሊበራል ዲሞክራሲ የሚመሩ ናቸው፡፡ ለምሳሌ፡ ቦትስዋና፣ ጋና፣ ሞሪሸስና ሌሎች፡፡

ኢህአዴግ ሊበራል ዲሞክራሲን የሚጠላበት ምክንያት የመንግስት ተፅዕኖና ጡንቻ ስለሚገድብ ነው፡፡

  1. ሊበራል ዲሞክራሲ አብዛኛውን የሐገራችን ወጣት የኢህአዴግ የኢኮኖሚ ጥገኛ እንዲሆን አያስችልም:
  2. ሊበራል ዲሞክራሲ የኢህአዴግ መንግስት የኢኮኖሚውን አውታር ሁሉ በእጁ አስገብቶ ስራ ለመቀጠርና ማንኛውም የኢኮኖሚ ጥቅም እንድታገኝ አባልነትን እንደመስፈርት እንዲጠቀም አያስችለውም:
  3. ሊበራል ዲሞክራሲ በነፃ ውድድርና በስራ እንጂ ኢህአዴግ የራሱን ባለሀብቶች እንዲፈበርክ አያስችለውም:
  4. ጥቃቅንና አነስተኛ፣ ማሕበራት ምናምን እየተባሉ ወጣቱን በብድርና በሌላ መልክ ሁሉ ለመቆጣጠርና ህሊናውንና ኪሱን ለመግዛት ሊበራል ዲሞክራሲ ምቹ አይደለም፡፡

ሊበራል ዲሞክራሲ ከጎዳም የሚጎዳው መንግስታትን እንጂ ህዝቡን አይደለም፡፡

እስቲ አስቡት፡ አሁን ለምሳሌ መብራት ሐይል የግል ቢሆን ለ 5 ደቂቃም መብራት ቢቋረጥ ለደረሰብህ ጉዳትና ኪሳራ ካሳ ትጠይቃለህ፣ ሕግም ይፈቅድልሀል፡፡ በመንግስት እጅ ግን አንድ ዐመትም ቢጠፋብህ አልቅሰህ ዝም ማለት ነው- በተለይም በኛ ሐገር ባለው ነባራዊ ሁኔታ፡፡ ቴሌም እንዲሁ የግል ቢሆንና በርካታ ተወዳዳሪዎች ቢመጡ እንዲህ ይጫወትብን ነበር ባንኮችስ ቢሆኑ ሌሎች የመሰረተ ልማቶችም ቢሆኑ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ይሰሩ ነበር፡፡

ሀገር የምታድገው የሐገሪቷ ነዋሪዎች ገቢ ሲያድግ፣ ኢንተርፕረነሮች ሲበዙ፣ ኢንዳስትሪ ሲስፋፋ እንጂ በቢሮክራሲና በሙስና የተሸበበ መንግስት ህዝብን አራቁቶ ሀብቱን ሁሉ ሰብስቦ ዘላቂና እውነተኛ እድገት ያመጣል ብሎ ማሰብ የሚቻል አይመስለኝም፡፡

የኢህአዴግ በሊበራል ዲሞክራሲ ላይ ያለው የከረረ ጥላቻም ከራሱ ጥቅም አንፃር ብቻ ነው፡፡ ህዝቡን በተለይም ወጣቱን በተለያየ ዘዴ የመንግስቱ የኢኮኖሚ ጥገኛ በማድረግና ሌላ ነገር እዳያስብ ኪሱም አእምሮውንም መስለብ፡፡ በውጤቱም የኢህአዴግ ዕድሜ ማርዘም፡፡

ሊበራል ዲሞክራሲ የሚያስፈራው መንግስታትን በተለይም ጨቋኝ መንግስታትና ይሀንን ጭቆና ማራዘም የሚፈልጉትን እንጂ ህዝብን አይደለም፡፡

 
Leave a comment

Posted by on October 25, 2014 in Uncategorized

 

Leave a comment